ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አ.ማ በሞጆ ከተማ ያስገነባቸውን አንድ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጽ/ቤት ህንፃ እና ሁለት የማኅበረሰብ መዝናኛ የንግድ ቤቶች፣ የሞጆ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ መሰረት አሰፋ፣ የዩናይትድ ቤቨሬጅስ አ.ማ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤፍሬም ይርጋ እንዲሁም ሌሎች የሞጆ ከተማ አስተዳደርና የዩናይትድ ቤቨሬጅስ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም አስመርቋል።
ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጽ/ቤት ህንጻ 7 ክፍሎችና አንድ የጥበቃ ቤት ያካተተ ሲሆን ሁለቱ የማኅበረሰብ መዝናኛ ቤቶች ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ የንግድ ቤቶች ሲሆኑ እያንዳንዳቸው 45 የሞጆ ወጣቶችን የስራና የሀብት ባለቤት ማድረግ ችለዋል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሞጆ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ መሰረት አሰፋ፣ ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አ.ማ ከተቋቋመ አጭር ጊዜው ቢሆንም ለአካባቢው ማኅበረሰብ በሚያደርገው ተከታታይ ድጋፍ በቀዳሚነት እንደምሳሌ የሚጠቀስ ድርጅት ነው ብለው፤ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ከ200 በላይ ወጣቶችም የተረከቧቸውን የንግድ ቤቶች ለስኬት በማብቃት ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማስመስከር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዩናይትድ ቤቨሬጅስ አ.ማ ስራ አስኪያጅ አቶ ተሬሳ ኡርጌሳ እንደዚሁ፣ ዩናይትድ ቤቨሬጅስ ከምስረታው ጀምሮ ተፈናቃዮችን በማቋቋም፣ በኮቪድ19 ለተቸገሩ የሞጆና አካባቢው አቅመ ደካሞች 1.2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የምግብ እህሎችን በመደገፍ፣ ለ286 ቤተሰቦች አመታዊ የጤና መድኅን ክፍያቸውን በመሸፈን፣ ለ2000 አቅመደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች በማሟላት እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ የስራ እድል በመፍጠር እስካሁን ያሳየውን አብሮነት ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው የፕሮጀክቶቹ ተረካቢ ለሆኑት ወጣቶች መልካም እድል ተመኝተዋል። የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤፍሬም ይርጋ በበኩላቸው፣ ማኅበረሰቡን በምንችለው አቅም ሁሉ መደገፍ የሁልጊዜም ትኩረታችን ነው ያሉ ሲሆን፣ ለፕሮጀክቶቹ ስኬት ትብብር ላደረጉ አካላት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
Comments