ድርጅታችን ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አ.ማ በሃገር ውስጥና በውጪ ባለሃብቶች በጋራ ጥምረት በ88 ሚሊዮን ዩሮ የመነሻ ኢንቨስትመንት የተቋቋመ ሲሆን የመጀመሪያ ምርቱ የሆነው አንበሳ ቢራ በላቀ ጥራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የገበያ ድርሻውን እያሳደገና ስኬታማነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።
ወቅቱ ሀገራችን በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ያለችበት መሆኑን ሁላችንም የምንረዳው ነው። በአንድ በኩል የኮቪድ19 ወረርሺኝ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ስጋት ሲሆን በሌላ በኩል የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ቦታዎች ርብርብ እየተደረገ ነው። ሆኖም የነገይቱ ኢትዮጵያ ባለቤት የሆኑትን የዛሬዎቹን ህፃናትና ታዳጊዎች ማስተማርና ለዚህም አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ዩናይትድ ቤቨሬጅስ ይገነዘባል። ለዚህም ነው የመማር ማስተማር ስርዓት መጀመሩን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የሞጆና አካባቢዋ ተማሪዎች በዛሬው እለት 24,000 ደብተሮችና 2,500 እስክርቢቶዎችን ልናበረክት የወደድነው።
ድርጅታችን ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አ.ማ ከሞጆና አካባቢው ነዋሪዎች የተነጠለ እድገት ጤናማ ይሆናል የሚል እምነት የለውም። በዚህ አቋሙም፣ ቀደም ሲል ኮቪድ19 ያስከተለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚደረገው ርብርብ አጋር በመሆን ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለተቸገሩ የሞጆ ነዋሪዎች የሚሆኑ የምግብ ምርቶችን እንዲሁም የድርጅታችን መስራች በሆነው ካንጋሮ ፕላስት በኩል ደግሞ ሁለት(2) ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ፍራሾችን ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ 1.5 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለሞጆ ከተማ አስተዳደር የኮምዩኒቲ ፖሊሲንግ ቢሮ በመገንባት ላይ እንገኛለን።
የነገዋን ኢትዮጵያ በትጋትና በቅንነት የሚያገለግሉ ሃገር ተረካቢዎች እንደሚሆኑ አንጠራጠርም። ወደፊትም ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አ.ማ አንበሳዊ በሆነው የመደጋገፍና የመተባበር እሴቱ በሚችለው አቅም ሁሉ የሞጆን ከተማ ልማት በሚደግፉና ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ሁሌም ከከተማ አስተዳደሩ ጎን እንደሚሆን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፤ እናመሰግናለን።
Comments